ወቅታዊ መልእክት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

ኦርቶዶክሳዊ የቤዛነት ትምህርት በብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የኢጣሊያ እና አካባቢ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ኦርቶዶክሳዊ የቤዛነት ትምህርት በአጭሩ

ቤዛ የሚለው የቃሉ ትርጉም፦ መድኀኒት፣ የተያዘ ማስለቀቂያ ገንዘብ/ዋጋ፣ ምትክ፣ ለውጥ፣ አዳኝ፣ ታዳጊ፣ ዋስ፣ ተያዥ፣ ፈንታ፣ ካሳ፣ የሕይዎት ዎጆ ጋሻ

ተብሎ በየመዘገበ ቃላቱ ተተርጉሞ ይገኛል።

ለምሳሌ ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ በሀገራችን በወረደው የአፈና እና የዕገታ መቅሠፍት ምክንያት የሚታፈኑ ሰዎችን ለማሰለቀቅ ለአፋኞች የሚከፈለው ገንዘብ ቤዛ ይባላል። (ምሳ 13፥8)። ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ከተወሰድንበት፣ ከታገትንበት፣ ከሲኦል እስር ቤት ከአጋንንት ከበባ ከኃጢአት ሰንሰለት ለማስለቀቅ የከፈለው ግን ቁሳዊ ገንዘብ ሳይሆን ክቡር ሕይወቱን ነው።

ዘዚአነ ሞተ ነሥአ ወእንቲአሁ ሕይወተ ወሀበነ

ትርጉም

የእኛን ሞት ተቀብሎ የእርሱን ሕይወት ሰጠን

እንዳለው ቅዱስ ኤፍሬም።

እራሱም መድኀኒታችን ቤዛችን ክርስቶስ ስለቤዛነት አገልግሎቱ

እስመ ኢመጽአ ወልደ እጓለ እመሕያው ከመ ይትለአክዎ ዘእንበለ ዳዕሙ ከመ ይትለአክ ወየሀብ ነፍሶ ቤዛ ብዙኀን

ትርጉም

የሰው ልጅ ሊያገለግል ሰውነቱንም ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም (ማቴ 20፥28) ሲል ተናግሯል።

የሰው ልጅ እንዲያገለግሉት ሳይሆን ለማገልገልና ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ለመስጠት መጥቷል አለ። ቤዛ የሚለው ቃል ግሪኩንም የሚያውቁ አመሳክረው እንደሚናገሩት ብዙውን ጊዜ የሚያመለክተው ባሪያን ለመዋጀት የሚከፈለውን ዋጋ ነው። ክርስቶስም እኛን ከኀጢአት ባርነት ነጻ ለማውጣት የገዛ ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ከፈለ፡፡ ለብዙዎች የሚለው አገላለጽም የክርስቶስ ሞት በሰዎች ምትክ መሆኑን በአጽንኦት ይገልጻል።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም  በተመሳሳይ

መጠወ ርእሶ ቤዛ ኵሉ ወኮነ ሰማዕተ በዕድሜሁ

ትርጉም

ክርስቶስ ራሱን ለሁሉ ሰው ቤዛ አድርጎ ሰጠ(1ጢሞ 26)

ወይም ሰዎችን ሁሉ ከኃጢአት ለመዋጀት ራሱን ቤዛ አድርጎ የሰጠ እርሱ ነው ፤ ይህም ትክክለኛው ጊዜ ሲደርስ የእግዚአብሔርን የማዳን ፍላጎት የሚያስረዳ ምስክርነት ነው የሚል ሲሆን ይህም ድኅነት የቀረበው ለሰው ሁሉ እንደ ሆነ ያመለክታል፡

ቤዛነት ለፍጡር የሚሰጥ ወይም የማይሰጥ የሚሰበክ ወይም የማይሰበክ እንደሆነ ለመረዳት መጀመሪያ የእግዚአብሔርን ባሕርያት ማወቅ ይጠቅማል።

የእግዚአብሔባሕርያትም

) ተሻጋሪ (transitive/communicable attributes of God) እና

፪)የማይሻገሩ(intransitive/incommunicable attributes of God) ተብለው በሁለት ይከፈላሉ። በእነዚህ ሁሉ ሥላሴ አንድ ናቸው።

የሚሻገሩና የማይሻገሩ የእግዚአብሔር ባሕርያት

እነዚህን ለይቶና ጠንቅቆ ማወቅ የራስን ጉሥዐተ ልብ የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ አስመስሎ በድፍረት ከመናገር፣ ስቶ ከማሳት፣ ተጠራጥሮ ከማጠራጠር እና ተሰናክሎ ከማሰናከል ይጠብቃል።

እመቤታችንና ሌሎቹንም ቅዱሳን የፈጣሪያቸው ተቀናቃኞች አድርጎ ከማሰብና አልፎም ለሕዝብ መሰናክል ከመሆን ያድናል። ለምእመናን ከሃይማኖት መንገዳቸው ላይ የኑፋቄ ወጥመድ እና መሰናክል ማሰቀመጥ ደግም ከአርዕስተ ኃጣውዕ መካከል የሚቆጠር ወዮታ ያለበት መሆኑን ጌታችን

በእኔም ከሚያምኑ ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ሁሉ፥ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ጥልቅ ባሕር መስጠም ይሻለው ነበርበእርሱ ጠንቅ ማሰናከያ ለሚመጣበት ለዚያ ሰው ወዮለት(ማቴ 18፥16)  ሲል አስጠንቅቋል።

፩) የማይሻገሩ የእግዚአብሔር ባሕርያት (Intransitive Attributes of God)

ለፍጡራን ከማይስማሙ የብቻው ሆነው ከሚቀሩ ባሕርያቱ መካከል፡-

  • Omnipresent በአንድ ጊዜ በሰማይና በምድር መሙላት ወይም በሁሉም ቦታ መገኘት
  • Omniscient ሁሉን አዋቂነት
  • Omnipotent ምንም የማይሳነው ሁሉን ቻይነት
  • Immutable አለመለወጥ
  • Self-existence በራሱ መኖር
  • Eternity እና ዘላለማዊነት

የመሳሰሉት ናቸው።

ፍጡር የቱንም ያህል በተጋድሎ ቢበረታ፣ በቅድስና ቢያድግና ዐሥሩ ማዕርጋትን ቢያሟላ ከእነዚህ የእግዚአብሔር ባሕርያት ሊካፈል አይችልም።

፪) ተሻጋሪ የእግዚአብሔር ባሕርያት (Transitive Attributes of God)

ከተሻጋሪ ባሕርያቱ መካከል ደግሞ እግዚአብሔር፦ ቅዱስ፣ ፍቅር፣ ጻድቅ፣ ቸር፣ መሀሪ፣ ርኅሩኅ፣ ታማኝ፣ እውነተኛ፣ ታጋሽ ጥበበኛ ወዘተ ነው።

የባሕርይ አምላክ መሆን ባንችልም እነዚህን ተላላፊ ወይም ተሻጋሪ ባሕርያቱን በመኮረጅ እርሱን መምሰል እንድንችል ፈቅዶልናል፤ በተወሰነ ደረጃ ከእነዚህ ባሕርያቱ ለፍጡራን ማለትም ለመላእክትና ለሰዎች ሰጥቷል። ክርስቶስን ስለመምሰል ስንነጋገር በዚህ መንገድ ነው። ለአስረጂነትም ጌታ በወንጌልየተናገረውን  መመልከት ይጠቅማል

እንግዲህ የሰማዩ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተ ፍጹማን ሁኑ “ ማቴ 5:48

ፍጹምነት ከእግዚአብሔር ለሰዎች የተፈቀደ ትሻጋሪ ባሕሪይ መሆኑን ልብ ይሏል

ቤዛነትም/አዳኝነትም እንግዲህ  ከተሻጋሪ ባሕርያቱ መካከል የሚገኝ በመሆኑ ለድንግል ማርያም በሰፊው ለሌሎች ቅዱሳንም በደረጃቸው ተሰብኮና ተሰጥቶ በቅዱሳት መጻሕፍት ይገኛል። አልፎ ተርፎ ሰውን ከአደጋና ከሌላም በልዩ ልዩ መንገድ ከሚጎዳው ነገር ለሚከላከሉለት ቁሳቁስ ለገንዘብ፣ ለጥላ፤ ለባርኔጣ ለጫማ ለጋሻ ወዘተ ይነገራል። ገንዘብ እንዴት ቤዛ እንደሆነም ወቅታዊ የሀገራችንን ሁኔታ እንደምሳሌ በማቅረብ ከላይ አስረድተናል።

ከጥንት ቅዱሳን ሊቃውንት መካከል በአንዱ በቅዱስ ጎርጎርዮስ

እም ሆሣዕናሁ አርአየ ተአምረ ወመንክረ ዘኢተገብረ እምቅድመ ወዘኢይከውንሂ እምድኅረ

ትርጉም

ከመድኀኒትነቱ የተነሣ ከዚህ ቀድሞ ያልተደረገ ወደፊትም የማይደረግ ድንቅ ተአምራቱን አሳየ

እንደተባለው የጌታችንን ቤዛነት ልዩ የሚያደርጉት በረካታ ሁኔታዎች ቢኖሩም ለምሳሌ እራሱን አሳልፎ ለዓለም ድኅነት ያውም ለጠላቶቹ ውድና ክቡር ሕይወቱን አሳልፎ መስጠቱ ልዩ ያደርገዋል፤ ከመድኀኒትነቱ የተነሳ እንደተባለው አምላክ ብቻም ቢሆን ሰው ብቻም ቢሆን አንድንም ነበርና ሰውም አምላክም ሆኖ ያዳነን ስለሆነ የእርሱን ቤዛነት ልዩ ያደርገዋል።

ይሙት ቤዛነ በትስብእቱ ወየሀበነ መድኃኒተ ዘከመ መለኮቱ

እንዲል በሥግው ቃልነቱ የተቤዠን በመሆኑ ልዩ ቤዛነት/ መድኀኒትነት ነው። ምንም በድንግልና ፀንሳ በድንግልና ብትወልደው በአንድ ጊዜ ሰውም አምላክም መሆንን የሚጠይቀውን ይህንን የሥግው ቃል ቤዛነት መልዕልተ ፍጡራን የሆነች ድንግል ማርያም እንኳ አትደርሰበትም። አምላክነት የሌላት በአምላክነቱ ፈጣሪዋ ሲሆን በሰውነቱ የወለደችው ሰብአዊት ናትና ቤዛነቷ የልጇን ቤዛነት አይተካከለውም። ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይህንን ጠንቅቃና ለይታ ታስተምራለች።

ይሁን እንጂ ቤዛነቱ/መድኀኒትነቱ ከተሻጋሪ ባሕርያቱ መካከል ስለሆነ ለእናቱ ለቅድስት ድንግል ማርያም ከእናትነቷ የተነሳ ቤዛዊተ ዓለም እንድትባል ፈቅዶና ወዶ ያደላት ያሳተፋት እንጂ ተቀናቃኙ አይደለችም።

ንጽሕተ ንጹሐን ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም አእምሮ ላለው ሰው ምልጃዋን፣ ቃል ኪዳኗን፣ ስደቷን መከራ መቀበሏን ሁሉ አቆይቶት የቤዛ ዓለም ክርስቶስ እናት በመሆኗ ብቻ እንኳ ቤዛዊተ ዓለም መባል ቢያንሳት እንጂ እንደማይበዛባት ይረዳል።

ሙሴም የእስራኤል ቤዛ ቢባል፣ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖትም የኢትዮጵያውያን ቤዛቸው ቢባል የጌታችንን ቤዛነቱን የሚቀንሱበት ወይም የሚሻሙት አይደሉም። እርሱም እንደ ቤተሰብ እንጂ እንደ ተቀናቃኝ ወይም እንደ ባላንጣ አይመልከታቸውም።

ድንግል ማርያምም ሆነች ሌሎች ቅዱሳን የባሕርይ ንጉሥ እርሱ ከእርሱ ቀጥሎ በሰጣቸው ሥልጣን የመንግሥቱ ታማኝ አገልጋዮች ከእርሱ ቀጥለው ያሉ የመንግሥቱ ባለ ሥልጣናት እንጂ የመንግሥቱ ገልባጮች አይደሉም። ይህ አስተሳሰብ ደዌ ሰይጣናዊት በተባለች በፍቅረ ሲመት በሽታ የሚሠቃይ የዘመኑ ትውልድ አስተሳሰብ ነው። በእግዚአብሔርና በቅድስት ድንግል ማርያም በሌሎቹም ቅዱሳን መካከል ባላንጣነት የለም።

   ቤዛ፦ ዋጋ/የተያዘን ነገር ለማስለቀቅ የሚከፈል ገንዘብ፣ ምትክ፣ ለውጥ፣ ካሳ፣ ተያዥ በሚለው ትርጉሙ ሁሉ ጌታችን በአዳም ተተክቶ ወይም ተገብቶ ያደረገውን የእውነተኛ ፈራጅነቱንና የችርነቱን ሥራ ሁሉ ጠቅልሎ በሁለት ፊደላት የያዘ በጣም ያጠረ ቃል ሲሆን ሲፈታ ዓለምን ይመላል።

ዳግማይ አዳም ከመ ያግብኦ ለአዳም ቀዳሚ ብእሲ እምድር ውስተ ገነት፤ ሥኢሮ ፍትሐ ሞት

ትርጉም

“ የሞት ፍርድን አጥፍቶ የቀደመ ሰው አዳምን ከሲኦል ወደገነት ከኀሳር ወደክብር ይመልሰው ዘንድ እመቤታችን ባንቺ ባሕርይ ተወልዷልና ተፈሥሒ ደስ ይበልሽ”

እንዲል ቅዱስ ኤፍሬም ሕይወቱን በመያዣነት ሰጥቶ ሕግ ከሚጠይቀው ዕዳ ነጻ አድርጎታልና። እንዲሁም

ወቦአ እግዚእ ኢየሱስ  ውስተ ኩሉ ጸዋትወ መከራ እንተ ባቲ አመከረነ ጸላኢ

ትርጉም

“ጌታ ኢየሱስ ጠላት ያመጣብንን ሁሉ ልዩ ልዩ መከራ  ተቀበለልን”

እንዲል ከላይ የተገለጹት ቤዛ የሚለው ቃል ትርጉሞች ሁሉም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ተፈጽመዋል።

እመቤታችን ቤዛዊተ ዓለም መባል ይገባታል!

ከእርሷ በቀር ዳግሚት ሔዋን የሚባሉ ቅዱሳት አንስት የሉምና፤ ሰው ሁሉ በጥንተ አብሶና በግል ኃጢአት ምክንያት የእርግማን ተሸካሚ በሆነበት ዘመን በእግዚአብሔር ፊት በሚቆመው በመጋቤ ሐዲስ ቅዱስ ገብርኤል አንደበት ቡርክት አንቲ እምአንስት የተባለች እርሷ ብቻ ናትና፤ ሰው ከእግዚአብሔር ፊት በኮበለለበትና ከሰይጣን ጋር በተሻረከበት እግዚአብሔርም አዝኖ ከሰው በተለየበት ዘመን እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነውና ደስ ይበልሽ፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነትን አግኝተሻልና አትፍሪ፤ ወንድ አለማወቅሽ አያሳስብሽ እንበለ ዘርዓ ብእሲ ፀንሰሽ እንድትወልጅ ምሥጢረ ተዋሕዶን የሚፈጸመው መንፈስ ቅዱስ ወደ አንቺ ይመጣል የተባለች እርሷ ብቻ ናትና፤ ጸጋን የተመላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ የተባለች እርሷ ብቻ ናትና። የተመላችውም ጸጋ ቤዛነትን ይጨምራልና። አብሣሪዋ መልአክ ይህንን ሁሉ ምስጋና ቢያስቀድምም ተከራክራና ጠይቃ ለጥያቄዋ እውነተኛና ተገቢ መልስ ካገኘች በኋላ እኔ የእግዚአብሔር ባሪያው ነኝ፤ ነገር ግን በገለጽከው መሠረት ከሆነ የሚሳነው ነገር ባለመኖሩ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ ብላ መቀበሏ ብቸኛ መዳኛችን ለሆነው ሥጋዌው በር ከፋች ነውና ቤዛ ያሰኛታል።

እንደ አምላክነቱ አዳነን እንደሰውነቱ ካሳ ሆነልን እንዲሉ መጻሕፍት አዳኝ መለኮትና ካሳ ትስብእት በማኅፀኗ እንዲዋሐዱ ፈቃደኛ በመሆን ለዓለም ደኅነት ትልቅ ድርሻ አበርክታለችና፤ በልጇ  የማዳን/የቤዛነት ሥራ ውስጥ ሰፊ ደርሻ አላትና፤ ከወለደችው በኋላም ያላሰበችው ብዙ ጸዋትወ መከራ ቢደርስባትም ተነግሮ የማያልቀውን ያን ሁሉ መከራ ለዓለም ድኅነት ብላ በአኮቴት ተቀብላዋለችና ቤዛዊተ ዓለም ብትባል ቢያንስባት እንጂ አይበዛባትም። በግብረ ሕማማት የተጻፈውን ላሀ ማርያም የተባለውን የዕለተ ዐርብ መከራዋን ለሚያስብ  የስደቷን አስከፊነት ለሚያስተውል ክርስቲያን ቤዛዊተ ዓለም ብትባል የቤዛነት/ማዳን ሥራው ተካፋይ እንጂ የአምላክነቱ ተካፋይ አያሰኛትምና ተመዝነው በቀለሉ ግለሰቦችና ድርጅቶች ሳይናወፁ በቆየው ጤናማ ትምህርት መጽናት ይገባል።

ምትክ በሚለው የቤዛ ትርጉም አንፃርም፦ ሰላም ለኪ ሔዋን ንግሥተ ሰማይ ወምድር

በምትል አንዲት የሸንገላ ቃል በቀላሉ በተታለለችው ቀዳሚት ሔዋን ፈንታ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ያቀረበላትን ግሩም ግሩም ቃለ አክብሮና ቃለ አጋኖ ሁሉ እንደ ወረደ ያልተቀበልች ይልቁንም የመሰቀል ልጇ ፍቁረ እግዚእ ዮሐንስ

ወዳጆች ሆይ፥ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፥ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደ ሆነ መርምሩ” ( 1ኛ ዮሐ 4፥1)

እንዳለው የመልአኩ ገብርኤልን እያንዳንዱን ንግግሩን በርብራ፣ መርምራና አበጥራ የተቀበለች የዚያችኛዋ የተላላዋ ሔዋን ምትክ ጠንቃቃዋ ዳግሚት ሔዋን ድንግል ማርያም የመጀመሪዋ ሔዋን ዕዳ ከፋይ ስለሆነች ቤዛዊተ ዓለም ብትባል ይስማማታል። እኛም ቤዛዊተ ዓለም እያልን የምንዘምርላት ኦርቶዶክሳውያን  የርሱን ቤዛነት ቀምተን ለእርሷ የሰጠን  ተብለን አንነቀፍም።

በእንተ ሔዋን ተዐፅወ ኆኅተ ገነት ወእንተ ማርያም ድንግል ተርኅወ ለነ ዳግመ

ትርጉም

በሔዋን ምክንያት የገነት በር ተዘጋብን በድንግል ማርያም ምክንያት ዳግመኛ ተከፈተልን”

ማለት እኮ ምትክ ፋንታ በሚለው ትርጉሙ ቤዛዊተ ዓለም እያላት ነው ቅዱስ ኤፍሬም። ይህ ጤናማ ትምህርት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ትምህርት በመደበኛነት ሲሰጥ የኖረ ያለ የሚቀጥል ሆኖ ሳለ ለፍጡር አይነገርም፣ አይሰበክም፣ አይዘመርም መባሉ ምን ታሰቦ ነው?

 ዋስ፣ ኃላፊ/ተያዥ  በሚለው የቤዛ ትርጉም አንፃርም፦ ቤዛዊተ ዓለም ብትባል በመፅነስ፣ በመውለድ፣ ሐሊበ ድንግልናን በማጥባት፣ ሔሮድስ ሊገድለው ሲፈልገው  ይዛ በመሰደድ በርሃ ለበርሃ የተንከራተተች፣ በረሀብና በጥም፣ በሐሩርና በቁር የተሠቃየች፣ ቤዛነቱ የባሕርዩ የሆነውን መድኀኒታችንን እስከ ዕለተ ዐርብ በችግር ያሳደገች ድንግል ማርያም በዚህ ሁሉ የመዳናችን ሥራ ተካፋይነቷ ቤዛዊተ ኩሉ ዓለም ብትባል ስሕትቱ የት ላይ ነው?

ከእርግማን፣ ከሞት፣ ከሲኦል ከጥንተ አብሶ ፍዳ እና ከምልዐተ ኃጢአት ባርነት አድኖናል ያድነናልም። ይህ ሁሉ የእኛ ክብርና የእኛ ድኅነት በአንድ ቀን አልተከናውነም። ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር የፈጀ ሂደት ነበረው። ይህን ሁሉ ዓመት የፈጀው የፍጹም ክብራችንና ነፃነታችን የቤዛችንና የድኅነታችን ዝግጅት እናቱ እንደመሆኗ ኃላፊነቱ እስከ ዕለተ ትንሣኤ ድረስ በእርሷ ላይ ወደቆ የኖረና በእርሷ አማካኝነት ለፍጻሜ የበቃ ስለሆነ ቤዛዊተ ኩሉ ዓለም እንላታለን።

እመቤታችንን ቤዛዊተ ዓለም አይደለችም የሚል መምህር መጀመሪያ ይማር፣ ሰባኪም ቦታ የለውም፣ የጌታችንን ቤዛነት በተመለከተ  አምላክ ብቻም ቢሆን ባልሞተም ነበር ሰው ብቻም ቢሆን መዳን ባልቻልንም ነበር፤ የዕሩቅ ብእሲ ደም ሊያድን አይችልምና እያለች በነገረ ሥጋዌዋ የምትራቀቅ

ወእምዝ ሶበ ርእየ ከመ ኢበቍዓ ለአድኅኖተ ዓለም ደመ ነቢያት ቅዱሳን እምደመ አቤል ጻድቅ እስከ ደመ ዘካርያስ ወልደ በራክዩ ፈነወ ለነ ወልዶ መድኅነ ወመቤዝወ ከመ ይባልህ ወይቤዙ ከጻድቁ

ትርጉም

ከአቤል ደም ጀምሮ እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ የፈሰሰ የነቢያት ደም ዓለሙን ለማዳን እንዳልበቃ እንዳልረባ እንዳልጠቀመ ባየ ጊዜ ቤዛ መድኃኒት የሚሆን ልጁን ቤዛ መድኃኒት አድርጎ ሰደደልን ፈጽሞ ያድን ዘንድ(ቅዳሴ ኤጲፋንዮስ ቁጥር 27)

እያለች የጌታዋን ቤዛነት ከድንግል ማርያም ቤዛነት ለይታና ከፍ አድርጋ በቅዳሴዋ ዘወትር የምታውጅ፣ ድምፅዋን ከፍ አድርጋ የምትሰብክ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ምንም እንደማታውቅ ለይታ እንደማታስተምር አድርጎ በሚዲያ ማጠልሸት ታላቅ በደል ስለሆነ ንስሐ መግባትና ለወደፊቱም መጠንቀቅ ያስፈልጋል። የሚችሉትንም ብቻ ማስተማር ይገባል።

ቤዛዊተ ዓለም አይደለችም አትባልምም ብሎ በእመቤታችን ላይ የሚናገር ዲያቆን፣ ካህን፣ ኤጲስቆጶስ፣ ጳጳስ ፓትርያርክ ሁሉ ሥልጣነ ክህነት የለውም።

እርሱ አስተምሬ፣ በንስሐ አንጽቼ፣ መሥዋዕት አቅርቤና ቀድሸ አቁርቤ ሰዎችን አድናለሁ፣  ኃጢአተኞችን ወክየ  ስለ በደለኞች ፈንታ መሥዋዕት ይዠ ስለነሱ ልማልድ በእግዚአብሔር ፊት እቆማለሁ  ለማለት ከቻለ

ርስት አንቲ ወሥሉጥ ስምኪ በኀበ እግዚአብሔር

ትርጉም

አንቺ ርስት ነሽ፤ ስምሽም በእግዚአብሔር ዘንድ የሠለጠነ ነው (ቅዳሴ ማርያም)

የተባለች  ድንግልማ እጅጉን እንዴት አትበልጥ? ጸጋን የተመላች ድንግልማ ይልቁን እንዴት ፋንታችን አትሆን! ካህናት በእዚአብሔር ዘንድ የኃጢአተኞች ወኪሎች ወይም ዋሶችና ተያዞች ሲሆኑ ነቢያት ደግሞ በሰዎች ዘንድ የእግዚአብሔር ወኪሎች ናቸው። የእርሱ ሥልጣነ ክህነት ይህንን የድኀነት ሥራ እንደሚፈጽም ካመነ የድንግል ማርያም ቤዛነትና መድኀኒትነት ከእርሱ ሥልጣነ ክህነት እንዴት ያንሳል!

እንግዲህ እኛ በጎ ጎዳና የሚያስተምሩ እነ ቅዱስ ያሬድን፣ እነቅዱስ ኤፍሬምን፣ እነ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫን፣ እነ አባ ሕርያቆስን፣ እነ አባ ጽጌ ድንግልን እንከተላለን። እነዚህ ሁሉ በቀጥታም በምሥጢርም ስለ እርሷ የጸጋ ቤዛነት ብዙ አስተምረዋልና።

ቤዛ ይኩነኒ ኪዳንኪ በገጸ ፈጣሪ ሥሉጥ፤ አመ ወርኀ ነጊድ የኃልፍ ወይፀራዕ ሤጥ

ትርጉም

የቃል ኪዳኗ እመቤት ሆይ በፈጣሪ ፊት ፍጹም ባለሟልነት ያለው ቃል ኪዳንሽ የንግድ ወራት አልቆ ወረት በተቋረጠ ጊዜ መጠጊያ ይሁነኝ።”

ሶበሰ ኪዳንኪ ምክንያተ ድኂን ኢሀሎ፤ ፈለገ እሳት ወደይን እም አስጠመ ኩሎ

ትርጉም

የመዳን ምክንያት የሆነ ቃል ኪዳንሽ ባይኖር፤ የእሳትና የሥቃይ ባሕር ሁሉን አስጥሞ በጨረሰ ነበር።

ይህንና የመሰለውን ሁሉ እያሉ እንዳስተማሩን እነሱን እንሰማለን፤ አሰረ ፍኖታቸውን ወይም ፈለጋቸውንም እንከተላለን። እንግዲህ የቤዛነት ትምህርት ሰፊና ዓለምን የሚሞላ ስለሆነ ለጊዜው ከዚህ ማለፍ አይቻለንምና ከዚሁ ላይ ይቆየን።

በእውነትና በመንፈስ ስሙን እንቀድስ እናመልከውና ክብሩን እንወርስ ዘንድ የፈጠረን እግዚአብሔር ያለማቋረጥ የተመሰገነ ይሁን።

የደንግል ማርያምን ጣዕሟን ፍቅሯን በልቡናችን፤ ምስጋናዋን በአንደበታችን ይምላልን፤ ቃል ኪዳኗና ቤዛነቷ አጥር ቅጥር፣ ጋሻና መከታ ሆኖ ከክፉ ሁሉ ይጠብቀን። አሜን ይሁን ይሁን።

1 thought on “ወቅታዊ መልእክት

  1. ቃለ ሕይወት ያሰማልን ብፁዕ አባታችን ቡራኬዎት ትድረሰኝ እጅግ ጠቃሚ ወቅታዊ ትምህርት ነው !

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *