ዜና

የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን መሪ የነበሩት የርዕሰ ሊቃነጳጳሳት ፍራንሲስኮስ የቀብር ሥነ ሥርዓት ተፈጸመ። (ሚያዚያ ፲፰ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም)

ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ የተለዩትና የሮም ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንን በአባትነት ሲመሩ የቆዩት የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስኮስ የቀብር ሥነ ሥርዓት የተለያዩ የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎችና ተወካዮች፣ የብዙ ሀገራት መሪዎችና ተወካዮች ምዕመናን በቫቲካን ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በተገኙበት በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት ሥርዓተ ቅዳሴ ከተከናወነ በኋላ ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል።
በሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ በወሰነው መሠረት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖትን በመወከል ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የጣሊያንና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዲዮናስዮስ የምሥራቅ ጎጃም; ጀርመንና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ መገኘታቸው ታውቋል።
ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የተላከውን መልእክትም ለቤተ ክርስቲያኗ ኃላፊዎች አድርሰዋል።
በሥርዓቱ ላይ የኢኩሜኒካል ፓትርያትክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ በርቶሎሚዮስ፣ የሶርያ ኦርቶዶክስ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አግናጥዮስ ኤፍሬም ሁለተኛን ጨምሮ የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎችና ሀገራት መሪዎችም በሥርዓቱ ላይ ይገኛሉ።

ዘገባውን ያደረሰን መምህር እስክንድር ከፈረንሳይ ነው

1 thought on “ዜና

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *